ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተሰጠ የድጋፍ መግለጫ

በአውሮፓውያን አቆጣጠር በሂውስተን ቴክሳስ በ1984 በአራት ቡድኖች የተመሰረተው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ዘንድሮ 35ኛ ዓመቱን በዳላስ ከተማ ያከብራል። ድርጅቱ በሰሜን አሜሪካ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከሀይማኖት ነጻ የሆነ ድርጅት ነው። ከግብር ነጻ የሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ የተመዘገበው በካሊፎርኒያ ክፍለ ሀገር ሲሆን ዓላማው ኢትዮጵያውያንን ከያሉበት ለማሰባሰብና ስፖርትን ተጠቅሞ የአገራችንን የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ውጭ ተወልደው ለሚያድጉት ልጆቻችን ለማስተማርና ለማውረስም ጭምር ነው።

ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ጊዜያት በአምባገነኖችና በዘረኞች ታፍኖ ለኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሟገት ለመብት ተቆርቋሪዎችም የመገናኛ መድረክ ሆኖ ኖሯል። በርሀብና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የገንዘብ አስተዋጾ ያደርጋል። በትምህርታቸው ጎበዝ ለሆኑ ተማሪዎች እርዳታ መስጠቱን ቀጥሏል:: በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካና በካናዳ የሚገኙ በአጠቃላይ 31 ክለቦች አሉት። በየዓመቱ የሚካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያንን የሚያገናኝ መዲና መሆኑ እርግጥ የሚያኮራ ነው።

ፌዴሬሽናችን አሁን በአገራችን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካዊ ለውጥ ይደግፋል። በተጨማሪም ድጋፋቸውን የወደፊት ብሩህ ተስፋቸውንና ምኞታቸውን ለጠቅላይ ምኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በነፃነት ለመግለጽ በወጡት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ በደረሰው ከፍተኛ አደጋ በጣም አዝነናል። ይህን በመልካም የተጀመረውን የሠላም የአንድነትና የፍቅር ጉዞ ለማደፍረስ ታስቦ የተደረገውን አፀያፊ ተግባር አጥብቀን የምናወግዘው መሆናችንን እንገልፃለን። ፈጣሪ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናቱን እንዲሰጣቸው እንለምናለን።

ዶክተር አብይ አሕመድ የብዙ አመታት የፍትህ እና የዴሞክራሲ መስዋትነት ለወቅቱ የላካቸው የለውጥ አቀንቃኝና የኢትዮጵያውያን መቃተት መልስ ናቸው ብሎ ተረድቶታል:: ከ40 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲናፍቀው የኖርነውን ኢትዮጵያዊነት አምባገነኖች ሊቀብሩት ከከተቱት ጉድጓድ አውጥተው ስላጎናጸፉን ከልብ የመነጨ ምስጋና እናቀርባለን። የጀመሩትንም የለውጥ ሂደት በእውነተኛ መሰረት ላይ ለመትከል እንዲቻል እኛም ያላሰለሰ ድጋፍ ለመስጠት በምንችለው ለመርዳት ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እንወዳለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ።

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ