ከኢትዮጲያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የተሰጠ ልዩ መግለጫ

Feb 26, 2024

ከኢትዮጲያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የተሰጠ ልዩ መግለጫ

Announcements | 0 comments

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮዽያውያን ስፖርትና ባሕል ፌዴሬሽን ከማናቸውም ሐይማኖታዊና ፖለቲካዊ ተግባራት ፍፁም ነፃ የሆነ ድርጅት ነው።

እንደ አንድ ሕጋዊ ድርጅት በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ በተደጋጋሚ እየተካሄደ ያለውን የተቀነባበረ የነፍስ ማጥፋት ዘመቻ አጥብቀን እናወግዛለን:: ሠላማዊው የኢትዮዽያ ሕዝብ በፈቀደው ሐይማኖትና የሥራ ዘርፍ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የማምለክና ቤተሰብ አፍርቶ የመኖር መብቱ ሊከበር እንደሚገባው በድጋሚ ለማሳሰብ እንወዳለን::

ሕይወታቸውን ያለአግባብ ላጡት መነኩሴዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ መምሕራን፣ የወደፊት ኢትዮጵያ ተረካቢ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎችና በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው ለነበሩ ሙያተኞች አሁንም ድምፅ ማሰማታችንን እንቀጥላለን:: ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው ፈጣሪ መጽናናቱን እንዲሰጣቸው እንለምናለን::

የኢትዮጵያውያን ህልውና ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ተወሳሰበ ችግር ስለሄደና ህዝብም በሠላም ወደ ተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል መዘዋወር አለመቻሉ አሳስቦናል። መንግሥትም በንፁሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸሙትንና የዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የሚያወግዙአቸውን አስከፊ ግድያዎች በግዜ ማስቆም አለመቻሉ የበለጠ አሳስቦናል። ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በበለጠ መንገድ ኢትዮጵያን ለማዳንና ሠላም ለኢትዮጵያውያን እንዲሰፍን በምንችለው ሁሉ እንድንረዳዳ በአክብሮት እንጠይቃለን::

ኢ-ሰብአዊና የዓለም መንግሥታት ሕግ የሚያወግዛቸው በዘር: በማንነትና በሐይማኖት ላይ ያነፃፀረ ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም::

የኢትዮዽያና የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ የሆኑትን ታሪካዊ ተቋማት ማውደም ይቁም::

ሠላም ለኢትዮጵያ ይሁን።

የኢትዮጵያ ስፖርትና ባሕል ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ

Share This