ከሰሜን አሜሪካ የኢትዮዽያውያን ስፖርትና ባሕል ማኀበር የተሰጠ ልዩ መግለጫ

Feb 5, 2023

ከሰሜን አሜሪካ የኢትዮዽያውያን ስፖርትና ባሕል ማኀበር የተሰጠ ልዩ መግለጫ

News | 0 comments

02-04-2023

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮዽያውያን ስፖርትና ባሕል ማኀበር ከማናቸውም ሐይማኖታዊና ፖለቲካዊ ተግባራት ፍፁም ነፃ የሆነ ድርጅት እንደሆነ የታወቀ ነው።

ሆኖም ግን በትውልድ ሐገራችን ኢትዮዽያ ኢ-ሠብአዊና የዓለም መንግሥታት ሕግ የሚያወግዛቸው በዘር፣ በማንነትና በሐይማኖት ላይ ያነፃፀረ ጥቃት በኢትዮዽያውያን ወገኖቻችን ላይ ሲደርስ የተበላሸው እንዲስተካከል፣ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ማስቆም የሚገባው የመንግሥት ክፍል ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፣ በሐገራችን ኢትዮዽያ የሕዝብ ሠላምና ደህንነት እንዲሰፍን የማኀበራችንን አቋም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንገልጽ ቆይተናል።

አሁንም በድጋሚ ሕይወታቸውን ያለአግባብ ላጡት፣ ለተፈናቀሉትና ከፍተኛ ሃዘን ላይ ስላሉት ኢትዮዽያውያን ወገኖቻችን ሐዘናቸው ሐዘናችን ስለሆነ ድምፅ ማሰማታችንን እንቀጥላለን።

ኢትዮዽያውያን ፈጣሪያቸውን እንደፈቃዳቸው እንዲያመልኩና በእምነት ተቋሞቻቸው ሕግና የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት እንዲስተዳደሩ መንግሥት አስፈላጊውን ዋስትና መስጠት እንደሚገባው እናውቃለን። በአንፃሩ ግን መንግሥት ጣልቃ በመግባት፣ የሕዝብን መብት በመጣስ፣ አላስፈላጊ ሁከት እንዲነሳ ምክንያት በማመቻቸትና ኢትዮዽያውያን ወደለየለት የእርስ-በርስ እልቂት እንዲገቡ እየገፋፋ ስለሆነ እጅግ በጣም አሳስቦናል።

በተጨማሪም መንግሥት በሐይማኖት ተቋማት ሥርአተ ሕግ ውስጥ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብና ለዜጎች የሚገባውን የሕግ እንክብካቤ በአክብሮት እንዲሰጥ እናሳስባለን።

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮዽያውያን ስፖርትና ባሕል ማኀበር ያለንን ጉልበታችንን ሁሉ በመጠቀምና በማስተባበር ካዘኑትና አሰቃቂ በደል እየደረሰባቸው ካሉት ኢትዮዽያውያን ወገኖቻችን ጋር በአንድነት እንቆማለን።

ሠላም ለሐገራችን ኢትዮዽያ ይሁን።

Share This