በወንድማችን ዘውዱ ታከለ ዜና እረፍት እጅግ ማዘናችንን እንገልጻለን

Oct 27, 2023

በወንድማችን ዘውዱ ታከለ ዜና እረፍት እጅግ ማዘናችንን እንገልጻለን

Announcements | 0 comments

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ መግለጫ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ በወንድማችን ዘውዱ ታከለ ዜና እረፍት እጅግ ማዘናችንን እንገልጻለን::

ዘውዱ ታከለ ከቀበና: አዲስ አበባ እስከ ላስ ቬጋስ: ኔቫዳ አሜሪካ ድረስ አገሩንና ኢትዮጵያውያንን በእግር ኳስ ስፖርት ያገለገለ ወንድማችን ነበር:: ዘውዱ ታከለ ከቀበሌ ውድድር ጀምሮ በትግል ፍሬ ቡድንና እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ አድናቆትን ካተረፉ የአጥቂ ቦታ ተጫዋቾች አንዱ ነበር:: ዘውዱ በተክለ ሰውነቱ ብቃት ብቻ ሳይሆን ለስልጠና የነበረው ፍላጎት ተወዳዳሪ እንዳልነበረው የሚነገርለት ተጫዋች ነበር:: በኳስ ሜዳ በፍጥነት: ቅልጥፍና: ጥንካሬውና ፀባዩ ምስጉን ነበር:: ዘውዱ በተጫወተበት ዘመን የተከላካዮችን ጉሸማዎች በፀጋ የሚያስተናግድ የተረጋጋ ባህርይ ነበረው::

ዘውዱ ታከለ አሜሪካን አገር በሎስ አንጀለስ: ካሊፎርኒያ እና በላስቬጋስ ኔቫዳ ወደ 40 አመታት ኖሯል:: በነዚህ ዘመናት በሙሉ ከእግር ኳስ ህይወት ሳይርቅ በተጫዋችነት: በአሰልጣኝነት: በቡድን መስራችና መሪነት የሎስ አንጀለስ ስታርስን: ዳሎልንና የላስ ቬጋስ ቡድኖችን አገልግሏል:: በሰሜን አሜሪካ ፌዴሬሽን ከተጫዋችነት: ቦርድ አባልነትና የስራ አስፈጻሚ ሆኖ አገሩንና ማህበረሰቡን በቅንነት አገልግሏል:: ዘውዱ ታከለ ለብዙዎቻችን መካሪ ግዜውንና ሃብቱን ሳይሰስት አካፋይ ነበር:: በሎስ አንጀለስም በላስ ቬጋስም የዘውዱ ቤት ለሁሉም ክፍት ነበር:: በእግር ኳስ ምክንያት ጏደኝነትንና መሰባሰብን ህይወቱ አድርጎ ኖሯል:: ዘውዱ ታከለ (ዜድ) ተግብብቶ ለመስራት የማይከብድ ተፈጥሮ እያለው ለአመነበት ነገር ደግሞ ብቻውን ለመቆም የማይፈራ ቁርጠኛ ሰው ነበር:: ዘውዱ ታከለ ላለፉት 14 አመታት በህክምና ሲረዳ ነበር:: ህመሙን የታገለበት ፅናት ለሁላችንም ኩራትም ትምህርትም ሰጥቶናል:: አምላኩ ላይ ተመክቶ ህመሙን በእሱ መጠን የታገለና በተቻለው ሙሉ ህይወትን የኖረ ግለሰብ ማግኘት ይከብዳል:: ዘውዱ በተቻለው መጠን ከአመታዊው ውድድሮቻችን ላይ ተገኝቷል:: ባሳለፍነው 40ኛ ዓመት ዝግጅት ላይ በዋይሊ: ቴክሳስም አብሮን ነበር:: ዘውዱ ታከለ መልካሙን ገድል ተጋድሎ ቢለየንም ትዝታው አብሮን ይኖራል::

በፌዴሬሽኑ ስም ለስፖርት ቤተሰቡ: ለወዳጅ ስጋ ዘመዶቹና ቤተሰቡ: ለውድ ባለቤቱ ወይዘሮ ዮዲት እግዚአብሔር መፅናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን!

Share This