በሜልቦርን ኦሎምፒክ ለቀናት ተጉዞ ሀገሩን የወከለው ገረመው ደምቦባ በ90 ዐመቱ አረፈ።

Feb 27, 2023

በሜልቦርን ኦሎምፒክ ለቀናት ተጉዞ ሀገሩን የወከለው ገረመው ደምቦባ በ90 ዐመቱ አረፈ።

Memoriam | 0 comments

ወቅቱ 1956 አውስትራሊያ ሜልቦርን ኦሎምፒክን ደግሣለች።በውድድሩ እምዬ ሀገራችን ስትሣተፍ መሪ ኮከብ የነበረው ገረመው ሀገሩን ወክሏል በብስክሌት ስፖርት።በተጨማሪም በአትሌቲክስ ስፖርት ተሣትፎ አድርጓል።አትሌት ገረመው በገጠመው ህመም ምክንያት ህክምና ሲከታተል ቢቆይም የካቲት 16 ከዚህ ዐለም በሞት ተለይቷል።
ታህሳስ 7/1925 በአ.አ የተወለደው ገረመው ደምቦባ በሜልቦርን ኦሎምፒክ በጎዳና የብስክሌት ግልብያ ውድድር 24ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ይህም ውጤቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ እንደነበር ታሪክ ያወሳል። በውድድሩ ላይ ከገረመው በተጨማሪ መስፍን ተስፋዬ፣ ፀሐይ ባሕታ እና መንግስቱ ንጉሴ መሣተፋቸውን ታሪክ ያወሣል። ኢትዮጵያ በብስክሌት በቡድን አራተኛ ወጥታለች።
17ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በጣሊያን ሮም እ.ኤ.አ በ1960 ሲደረግ ገረመው ቢሣተፍም በገጠመው ጉዳት ከውድድሩ ወጭ ሆኗል። በ1968 ቶኪዮ ኦሎምፒክ የብስክሌት ቡድኑ አሠልጣኝ በመሆን አገልግሏል።
እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1973 በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው ሁለተኛ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የብስክሌት ቡድን ይዞ በመጓዝ ወርቅ ይዞ ተመልሷል።
ገረመው ደንቦባ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ሁሉ ስኬታማ እንደሆነ ይነገርለታል።
በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ 26 ዋንጫዎች እና 32 ሜዳልያዎች ተሸልሟል።
አትሌት ገረመው ደምቦባ ለሀገሩ የማይረሣ ታሪክ ሠርቶ አልፏል።ፌደሬሽናችን በተደጋጋሚ በክብር የዘከረው ሲሆን ህልፈቱን ተከትሎ የተሰማውን ሀዘን ይገልፃል።ለወዳጅ ዘመዶቹም መፅናናትን ይመኛል።
Share This